ጉዞዬ የጀመረው በኢትዮጵያ ውስጥ በመጠባበቂያ ካምፖች ውስጥ ለ22 ዓመታት በመጠበቅ ላይ ነው። ገና ከሠባተኛ ክፍል ጀምሮ በዙሪያዬ ያሉትን ችግሮች ሳይ በልቤ ውስጥ አንድ ውሳኔ ተጠነሰሰ፡- ሐኪም እሆንና ማሕበረሰቤን ለመታደግ መስዋዕትነት መክፈል። ይህንን ሕልም እውን ለማድረግ ትምህርት ላይ ሙሉ አቅሜን ለዓመታት ግብዓት አደረግሁ። ነገር ግን በ2015 እ.ኤ.አ ችግሩ ከሕክምና በላይ እጅግ የላቀ መሆኑን ተገነዘብኩ። ዓሊያን የሚጠባበቀው ማሕበረሰብ እንዴት መውጫ በሌለው ወጥመድ ውስጥ እንደተያዘ አየሁ፦ በኢትዮጵያ እንደ “እሥራኤላዊ” እየተቆጠረ የትምህርት፣ የሥራና የሕክምና መሠረታዊ መብቱ የሚነፈግ ሲሆን በእሥራኤል ያለው ማሕበረሰብ ደግሞ በኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን ቤተሰብ በገንዘብ ለመደገፍ እየተገደደ በሁለቱም ሃገራት የድህነትና የስነ-ልቦና ችግሮችን ዑደት ፈጥሯል። ስለዚህም ማሕበረሰቤ ጊዜያዊ እርዳታ ብቻ ሳይሆን – የማንነትን ክብርና እድገት የተላበሠ ዘላቂነት ያለው መፍትሔ እንደሚያስፈልገው ተገነዘብኩ። በ2015 እ.ኤ.አ ከሙያዊም ሆነ ከግል እይታ አንጻር የተደቀኑብንን ተግዳሮቶች ዋና ዋና ምክንያት ለይቼ ለማዎቅ ችያለሁ፡- በካምፖች ውስጥ የሚጠባበቀው ማሕበረሰብ በትንሹ ከወርሃዊ የቤት ኪራይ ጀምሮ እስከ እሥራኤል ሃገር መግባት ትልቁ ሕልሙ ድረስ ኢኮኖሚያዊና ሕልውናዊ ቀውስ እያጋጠመው እንደሆነና በእሥራኤል ሃገር ያለው ማሕበረሰብ ደግሞ በወላጅና ልጅ መካከል ካለው የቋንቋ አለመግባባት ክፍተት ጀምሮ እስከ ቤተሰባዊ መቆራረጥና የመነፋፈቅ ጭንቀት ድረስ የስነ-ልቦናዊና ማሕበራዊ ችግር ተጋርጦበታል።